የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አሸባሪውና ዘራፊው የትግራይ ወራሪ ሀይል በጦርነቱ ወቅት ያደረሰውን ስነ-ልቦናዊና ቁሳዊ ውድመት ወደ ነበረበት እንዲመለስና በአካባቢው ማሕበረሰብ መነቃቃትን ለመፍጠር በርካታ የመልሶ ማቋቋም ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ በጦርነቱ ወቅት ጉዳት ደርሶባቸው ከነበሩ አካባቢዎች መካከል አንዱ በሆነው የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞንም በርካታ ድጋፎች ተደርገዋል፣ ስልጠናዎች ተሰጥተዋል እንዲሁም ጥናቶች ተካሂደዋል፡፡




የግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅም በበኩሉ በዞኑ ለሚገኙ የቀበሌ፣ የወረዳና የዞን የግብርና ባለሙያዎች እንዲሁም አመራሮች የስነ ልቦናና የሙያ አቅም ማጎልበቻ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከሰብል ልማት፣ ከአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ከተፈጥሮ ሀብትና ደን ልማት አኳያ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ ለአካባቢው ምቹ የሆኑና የተሻለ ምርት ሊሰጡ የሚችሉ የሰብል የአትክልት ዘሮችንና የማዳበሪያ ድጋፍ መደረጉን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ የማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ አቶ በየነ ደርሶ ገልጸዋል፡፡ በኮሌጁ በአጠቃላይ ከ750 ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ የአትክልትና ፍራፍሬ ዘርና ችግኝ፣ የደን ልማት ዘርና ቁሳቁስ፣ የሰብል ዘሮች (የጤፍ፣ ማሽላና ስንዴ) እና የማዳበሪያ ድጋፍ መደረጉን አቶ በየነ ጨምረው ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይ ነሐሴ 9 እና 10/2014 ዓ.ም በሰቆጣ ወረዳ ወለህ እና ፍቅረ ሰላም ቀበሌዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች የአቦካዶና የብርቱካን ችግኞች ስርጭት ተደርጓል፡፡
ከስርጭቱ በተጨማሪም የግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ የሆርቲ ካልቸር መመምህርና የትምህርት ክፍሉ ሃላፊ በሆኑት በአቶ ፈንታሁን አስራት አማካኝነት ሙያዊ ገለጻ ከተደረገ በኋላ የቀበሌና የወረዳ የግብርና ባለሙያዎችና አመራሮች በተገኙበት ሞዴል የችግኝ ተከላ ተካሂዷል፡፡ በእለቱ በዩኒቨርሲቲው በድጋፍ መልክ ለዞኑ የተሰጠና በወለህ ቀበሌ በሙከራ ላይ የሚገኝ የስንዴ ሰብል ጉብኝትም ተደርጓል፡፡